1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የረቡዕ፤ ሚያዝያ 30 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

አ.አ፥ የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ ማሽቆልቆሉ ተገለጠ፤ ወለጋ፥ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ ነቀምቴ ስታዲየም ንግግር አሰሙ፤ ናይሮቢ፥ በጎርፍ አደጋው ማግሥት የኮሌራ ወረርሺን ሥጋት አጭሯል፤ ጋዛ፥ የራፋሕ መሸጋገሪያ ሰብአዊ ቀውሱ ተባብሷል፤ ሞስኮ፥ ከዩክሬን ጉዳይ ፈረንሣይ እጇን እንድታነሳ ሩስያ አስጠነቀቀች፤ ማድሪድ፥ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ሪያል ማድሪድ ከባዬርን ሙይንሽን

https://p.dw.com/p/4fdtB

አርዕስተ ዜና

*ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነቷ በዓለም አቀፍ መስፈርት  ማሽቆልቆሉን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ዐስታወቀ ።  ድርጅቱ ባወጣው የ2024 ዓ.ም የመገናኛ አውታሮች ነፃነት ደረጃ ኢትዮጵያ ከ180 ሃገራት ወደ 141ኛ ደረጃ ማሽቆልቆሏን ዐስታውቋል ።  ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 130ኛ ደረጃ ዘንድሮ በ11 ደረጃዎች ዝቅ ብላ መገኘቷንም ዘገባው ያሳያል ። 

*የጎርፍ መጥለቅለቅ በርካቶችን የገደለባት ኬንያ የኮሌራ ወረርሺኝ ሥጋት አጫረ ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጎርፍ ብርቱ አደጋ ባደረሰባት ኬንያ ከዐርባ በላይ ሰዎች በኮሌራ የመያዛቸው ዜና እጅግ እንዳሳሰበው ዛሬ ዐስታውቋል ። 

*ደቡባዊ ጋዛ ሠርጥ በምትገኘው የራፋሕ መሸጋገሪያ ውስጥ ዛሬ የአየር ድብደባ መፈጸሙን፤ የተኩስ ድምፅ እና ፍንዳታዎችም መስማታቸው የርዳታ ተግባሩን ይበልጥ አስቸጋሪ እንዳደረገው የሰብአዊ ርዳታ ለጋሽ ሠራተኞች ገለጡ ።

*ሩስያ ማንኛውም ወደ ዩክሬን የተላከ የፈረንሣይ ጦር ዒላማ ውስጥ እንደሚገባ አስጠነቀቀች ። ከፈረንሳይ፣ ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ሥጋት ተደቅኖብኛል ያለችው ሩስያ የኒኩሊዬር ጦር መሣሪያ የማሰማራት ሥልታዊ ልምምድ ልታደርግ እንደሆነ ሰኞ ዕለት ማስታወቋ የጦርነቱን አድማስ እና መጠን እንዳያሰፋው አስግቷል ።  

ዜናው በዝርዝር

አ.አ፥ የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ ማሽቆልቆሉ ተገለጠ

ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ደረጃዋ ማሽቆልቆሉን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (Reporters Without Borders) ይፋ አደረገ ። ድርጅቱ ባወጣው የ2024 ዓ.ም የመገናኛ አውታሮች ነፃነት ደረጃ ኢትዮጵያ ከ180 ሃገራት ወደ 141ኛ ደረጃ ማሽቆልቆሏን ዐስታውቋል ።  ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 130ኛ ደረጃ ዘንድሮ በ11 ደረጃዎች ዝቅ ብላ መገኘቷንም ዘገባው ያሳያል ።  የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ድርጅት ዘገባ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ታይቶ ነበር ያለው የመገናኛ ብዙኃን ሥራ የነፃነት ዐውድ «በጎሳ ተኮር ግጭቶች እና የእርስ በርስ ጦርነቶች ሳቢያ ተቀልብሶ» አሳሳቢ ሁኔታ መፈጠሩን» ያትታል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በኅዳር 2022 የትግራይ ጦርነትን በይፋ ያስቆመው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ በጀመረው ግጭት የተነሳም ጋዜጠኞች በሥራችን ጥቃት ይደርስብናል  የሚል ፍራቻቸው  እንደገና መቀስቀሱን ዘገባው አትቷል ። ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 15 ጋዜጠኞች በእሥር ላይ መሆናቸውንም ገልጿል ። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የሚባል የጋዜጠኞች የሞያ ማኅበር አለ ማለት ባይቻልም ያሉትም ሀሳባቸውን እንዲያጋሩ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም ። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ጋዜጠኛ ግን ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ተጨባጭ መሆኑን እና በዚህ ወቅት  የጋዜጠኝነት ሥራ ፈተና ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል ።

«የሚዲያ ኢንዱስትሪ መጀመሪያ አካባቢ የመከፈት እድል ነበረው፥ ከዚያ በኋላ በጣም ጠቦ፥ ብዙ ጋዜጠኞች ታስረው፥ እየተዋከቡ  እንደውም የተዳከመበት ኹኔታ ነው ያለው »

ባለፈዉ ሳምንት ዐርብ የተከበረዉን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ የወጡ ዘገቦች እንደሚያመለክቱት፦ ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትን ለማክበር ከሚጥሩ ሃገራት ባጭር ጊዜ ዉስጥ የፕሬስ ነፃነትን ወደሚያፍኑ ሃገራት አሽቆልቁላለች ። የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራትን ጨምሮ  በአዲስ አበባ የሚገኙ 18 ኤምባሲዎች የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን አስመልክቶ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የንግግርና የመገነኛ ብዙኃን ዘርፍ ነፃነት «መሠረታዊ የሰዎች መብት በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባ» ጠቅሰው ነበር ። በዓለም የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ኖርዌይ አንደኛ ደረጃ ላይ ስትሰፍር፥ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በ39 ዝቅ ብላ የመጨረሻው 180ኛ ላይ እንደምትገኝ የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዘገባ ያመለክታል ።

ወለጋ፥ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ ነቀምቴ ስታዲየም ንግግር አሰሙ

ከፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ዛሬ ወደ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ነቀምቴ ስታድየም ውስጥ በተደረገ ሕዝባዊ ድጋፍ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ማሰማታቸውን የጠቅላይ ሚንሥትሩ ጽ-ቤት በማኅበራዊ ድረ-ገጹ ዐስታወቀ ።  ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ከአራቱም የወለጋ ዞኖች የተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውም ተዘግቧል ።  አራቱ የወለጋ ዞኖች ባለፉት አምስት ዓመታት ተደጋጋሚ ዉጊያ የሚደረግባቸዉ፥ ዘር ተኮር ጥቃትም በስፋት የሚከናወንባቸው አካባቢዎች ናቸዉ ።  በአካባቢው የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አስከባሪዎችና መንግስት «ኦነግ ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ ነገር ግን ራሱን የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት (OLA) ብሎ በሚጠራዉ ታጣቂ ቡድን መካከል ተደጋጋሚ ውጊያ የሚደረግበት ነው ። በዉጊያዉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠላማዊ ሰዉ አንዳንዴ በአሰቃቂ ርምጃ ተገድሏል፥ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሏል ። ነቀምቴ ከተማ ዛሬ ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ ውይይቱ ይካድ አይካሄድ ግን  የታወቀ ነገር አለመኖሩን የአሶሳው ወኪላችን ነጋሣ ደሳለኝ ዘግቧል ።  ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወር ሚያዚያ 2015 ዓ.ም በነቀምቴ ከተማ በመገኘት ኅብረተሰቡን ማወያየታቸው የሚታወስ ነው ።

ናይሮቢ፥ በጎርፍ አደጋው ማግሥት የኮሌራ ወረርሺን ሥጋት አጭሯል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጎርፍ ብርቱ አደጋ ባደረሰባት ኬንያ ከዐርባ በላይ ሰዎች በኮሌራ የመያዛቸው ዜና እጅግ እንዳሳሰበው ዛሬ ገለጠ ።  ጎርፉ ከፍተኛ አደጋ በፈጠረበት ምሥራቅ ኬንያ ውስጥ 44 ሰዎች በኮሌራ ተሐዋሲ መታመማቸውን ተመድ ዐስታውቋል ። የኮሌራ ወረርሺኙ እንዳይስፋፋም ተመድ በንቃት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሷል ። ኬንያ ውስጥ ከመጋቢት ወር ጀምሮ የጣለው ብርቱ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተነሳ 238 ሰዎች ሞተዋል፥ ሰባ አምስቱ የገቡበት ዐይታወቅም ። በመላ ኬንያ ጎርፉ ባደረሰው ጉዳት ከ235,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ። የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በጎርፉ ምክንያት ለአንድ ሳምንት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች በሚቀጥለው ሰኞ ዳግም እንደሚከፈቱ ይፋ አድርገዋል ። ዝናሙ በመቀነሱ እና አደጋም ስለማያስከትል ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ይመለሳሉ ብለዋል ። በጎርፉ ሕይወታቸውን ያጡትን ለማሰብ የፊታችን ዐርብ በመላ ሀገሪቱ መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ እና መጠነ ሰፊ የችግን ተከላ መርሐ-ግብር እንደሚጀመርም ዐስታውቀዋል ።   የሰሞኑ የጎርፍ አደጋ ከኬንያ ባሻገር በኢትዮጵያ እና ሶማሊያም ጉዳት ማድረሱ አይዘነጋም ።

ጋዛ፥ የራፋሕ መሸጋገሪያ ሰብአዊ ቀውሱ ተባብሷል

ደቡባዊ ጋዛ ሠርጥ በምትገኘው የራፋሕ መሸጋገሪያ ውስጥ ዛሬ የአየር ድብደባ መፈጸሙን፤ የተኩስ ድምፅ እና ፍንዳታዎችም መስማታቸው የርዳታ ተግባሩን ይበልጥ አስቸጋሪ እንዳደረገው የሰብአዊ ርዳታ ለጋሽ ሠራተኞች ገለጡ ። በአካባቢው በበጎ ፈቃደኝነት ሰብአዊ ርዳታ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ ሠራተኞች ወትሮ አስቸጋሪ የነበረው የሰብአዊ ድጋፍ ተግባር ይበልጥ መባባሱን ተናግረዋል ። «የልግስና ማእድ» የተባለው የበጎ ፈቃደኞች ቡድን አባል የሆኑት አዛ ናና የሁኔታው መባባስ ለነዋሪው ቀርቶ ለበጎ ፈቃደኞችም ሥጋት ማጫሩን ተናግረዋል ።  

«እዚህ የመጨረሻ ቀናችን ሊሆን ይችላል ። ራፋሕ ውስጥ ሁኔታዎች እጅግ ተባብሰዋል ። የጋዝ እና የነዳጅ እጥረት አለ፥ አንዳችም አማራች የለም ። ልክ እንደ እናም ሰዎች ካሉበት ቦታ የሚያወጣቸው ይሻሉ ። ተፈናቃዮችን ስንረዳ ነበር፥ አሁን እኛ ራሳቸን የሚረዳን አካል ያስፈልገናል ። »

«የልግስና ማእድ» የተባለው የበጎ ፈቃደኞች ቡድን በየቀኑ 30,000 ተፈናቃዮችን ይመግብ እንደነበር ይነገርለታል ። 80 ከመቶ የአካባቢው ነዋሪም የምግብ ርዳታ የሚያገኘው ከዚህ ቡድን ነበር ። እንደ ጋዛ የጤና ሚንስትር ከሆነ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሰብአዊ ድጋፍ በአካባቢው ለሁለተኛ ቀን ተቋርጧል ። እሥራኤል በደቡባዊ ጋዛ የከረም ሻሎም በኩል አዲስ የሰብአዊ ርዳታ መሸጋገሪያ መክፈቷን ዐስታውቃለች ። የእሥራኤል ጦር ሰሞኑን ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲለቅቁ በማስጠንቀቅ የራፋህ መሸጋገሪያን የተቆጣጠረ ሲሆን፤ በጋዛ እና ግብጽ ድንበር የራፋህ መሸጋገሪያ የእሥራኤል ታንኮች እንደሚርመሰመሱ ተዘግቧል ።

ሞስኮ፥ ከዩክሬን ጉዳይ ፈረንሣይ እጇን እንድታነሳ ሩስያ አስጠነቀቀች

ሩስያ ማንኛውም ወደ ዩክሬን የተላከ የፈረንሣይ ጦር ዒላማ ውስጥ እንደሚገባ አስጠነቀቀች ። የፈረንሣይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ በየካቲት ወር ውስጥ ጦር ሠራዊት ስለመላክ መናገራቸው ውዝግቡን እንዳስነሳው ይነገራል።  በወቅቱ ኤማኑዌል ማክሮ የሩስያ ማሸነፍ የአውሮጳ ተደማጭነትን ዜሮ ያስገባል ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር ። በዩክሬን ጦርነት የሚገደሉ የፈረንሳይ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ሩስያ ገልጣለች ። የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባዪት ማሪያ ዛካሮቫ፦ ፈረንሣይ ወደ ጦር ቀጣናው ብቅ ካለች የሩስያ ጦር ሠራዊት ዒላማ ትሆናለች» ሲሉ አስጠንቅቀዋል ። «ፓሪስ ይህን ያረጋገጠችም ይመስለኛል» ብለዋል ቃል አቀባዩዋ ።  ከፈረንሳይ፣ ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ሥጋት ተደቅኖብኛል ያለችው ሩስያ የኒኩሊዬር ጦር መሣሪያ የማሰማራት ሥልታዊ ልምምድ ልታደርግ እንደሆነ ሰኞ ዕለት ማስታወቋ የጦርነቱን አድማስ እና መጠን እንዳያሰፋው አስግቷል ።  ይህ በእንዲህ እንዳለም፦ ሩስያ እንደ ሰሞኑ ሁሉ የዩክሬን የኃይል ምንጭ አውታሮችን ትናንት ለዛሬ አጥቢያ በሚሳይሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች መደብደቧ ተዘግቧል ። ሩስያ ከጦርነቱ ቀጣና በርቀት ምዕራብ ዩክሬን ውስጥ የሚገኙ ሁለት ተቋማትን ጨምሮ የኃይል ማመንጫዎችን መምታቷም ተጠቅሷል ።

ማድሪድ፥ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ሪያል ማድሪድ ከባዬርን ሙይንሽን

በሻምፒዮንስ ሊግ የደርሶ መልስ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ዛሬ ማታ የጀርመኑ ባዬርን ሙይንሽን ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ ጋ ይጋጠማል ። ትናንት በነበረው ጨዋታ ሌላኛው የጀርመን ቡድን ቦሩስያ ዶርትሙንድ የፈረንሣዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን 1 ለ0 አሸንፏል ። በደርሶ መልስ የ2 ለ0 ውጤትቱም ቦሩስያ ዶርትሙንድ እንግሊዝ ዌብሌይ ስታዲየም ውስጥ ግንቦት 24 ለሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ማለፉን አረጋግጧል ። ባዬርን ሙይንሽን በሜዳው አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ባደረገው ግጥሚያ የተለያየው በሁለት እኩል ውጤት ነበር ። ዛሬ ማታ ሪያል ማድሪድን በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናቤዉ ይገጥማል ። ባዬርን ሙይንሽን ዛሬ ማታ ማሸነፍ ከቻለ፦ ሁለቱ የጀርመን ቡድኖች ለፍጻሜ በመድረስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 የነበራቸው ታሪክ ይደገማል ማለት ነው ። በወቅቱ በፍጻሜው ባዬርን ሙይንሽን ቦሩስያ ዶርትሙንድን በአሪዬን ሮበን የመጨረሻ ደቂቃ ግብ 2 ለ1 አሸንፎ ዋንጫ ወስዶ ነበር ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።