1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት የልማት እና ትብብር ሚኒስትሮች ስብሰባ ለዩክሬንና ፍልስጤም

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 2016

እስራኤል በራፋ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ እንዳሳዘናቸው የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ክስ ሲመሰርት ደስተኛ የነበሩ አባል ሀገሮች በእስራኤል መሪዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይታሰብ ሲያሳስቡ መሰማታቸው ግራ የሚያጋባ መሆኑን ቦሬል ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4fdet
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል
ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ክስ ሲመሰርት ደስተኛ የነበሩ አባል ሀገሮች በእስራኤል መሪዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይታሰብ ሲያሳስቡ መሰማታቸው ግራ የሚያጋባ መሆኑን ቦሬል ገልጸዋል።ምስል Press Office, Albania Premiership

የአውሮፓ ህብረት የልማት እና ትብብር ሚኒስትሮች ስብሰባ ለዩክሬንና ፍልስጤም

የ27ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች የልማት እና ትብብር ሚኒስትሮች ትናንት ብራስልስ ባካሄዱት ስብሰባ ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመቋቋም ከሚያስፈልጋት ወታደራዊ እርዳታ በተጨማሪ፤ ለዳግም ግንባታ እና የኢኮኖሚ ማሻሽያ ፕሮራም ተጨማሪ እርዳታ ለመስጠት እና በጋዛ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም መርጃ ድርጅትን ለመርዳት ተወያይተው ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

ስብሰባውን የመሩት የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፕ ቦሪየል ሲሆኑ፤ ሚስተር ቦርየል ከትናንት ወዲያ ሰኞ እዚሁ ብራስልስ የተካሄደውን እና ለዩክሬን በቂ የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ለማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ  የመከረውን ከ25 አገሮች የመጡ የ140 ፋብሪካዎችና ኩባንያዎች ተወካዮች የተሳተፉበትን የመከላከያ እንዱስትሪ መድረክንም መርተዋል።

የሚኒስትሮቹ ውሳኔ በዩክሬን ላይ

የትናንቱ ባብዛኛው የህብረቱ የልማት እና ትብብር ሚኒስትሮች የተሳተፉበት ስብሰባ ዩክሬንን በሚመለክት ያተኮረው ግን በዳግም  ግምባታ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ መሆኑን ሚስተር ቦርየል አስታውቀዋል። “በዩክሬን ጉዳይ ዋናው ነገር መንግስት ባቀረበው የዳግም ግንባታ እቅድ እና የማሻሻያ ፕርግራም ላይ መወያየት ነው” በማለት የአገሪቱ መሰረታዊ ልማት ፍጹም በሚባል ደረጃ የወደመ እና እየወደመ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጦርነት የወደመ መኖሪያ ቤት ዩክሬን
የአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች የልማት እና ትብብር ሚኒስትሮች በዩክሬን መልሶ ግንባታ እና የኤኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ተወያይተዋል። ምስል Thomas Peter/REUTERS

 ሚኒስትሮቹ በሚቀጥሉት አራት አመታት ለዩክሬን መርጃ በብድር እና እርዳታ ሊቀርብ የታሰበው 50 ቢሊዮን ዩሮ እንዴት እና በምን ሁኔታ ሊሰጥ እንደሚችል የተወያዩ ሲሆን፤ የአውሮፓ ኮሚሽንም እርዳታው እንዲለቀቅ የሚደግፍ የግምገማ ሪፖርት ያቀረበ መሆን ተገልጿል።

የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም መርጃ ድርጅትን መርዳት አስፈላጊነት

ፍልስጤምን በሚመለክት ሚኒስትሮቹ በከፋ ሁኔታ ባለው ሰብአዊ ቀውስ ላይ በመወያየት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉት ፍልስጤሞች ለመድረስ ፈጥኖ በመንቀሳቀስ አስፈላጊውን ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ የሚያስፈለግ መሆኑ እንደታመነበት ተነግሯል። አዲሱን የፍልስጤም አስተዳደር እንዴት መርዳት እንደሚቻልም ውይይት ተደርጓል ተብሏል።

የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ አዲስ የስደተኞች ሕግ አፀደቀ

ቀደም ሲል እስራኤል በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም መርጃ ድርጅት ላይ አቅርባው በነበረው ክስ ምክኒያት የርዳታ ለጋሾች ለድርጅቱ የሚሰጡትን እርዳታ አቋርጠው የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ውቅት ግን፤ የቀረበው የእስራኤል ክስ በገለልተኛ ቡድን ተጣርቶ ውድቅ የተደረገ በመሆኑ፤ ምንም አይነት ድርጅቱን ላለመርዳት የሚቀርብ ምክንያት እንደሌለ ቦርየል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

 “ለመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም መርጃ ድርጅት የሚሰጠውን እርዳታ ለማቋረጥ የሚቀርበው ምክኒያት መሰረት የለውም። በቀድሞዋ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ወይዘሮ ካትሪን ኮሎና የተመራው ገለልተኛ አጣሪ ቡድን የቀረበው ሪፖርት ሁሉንም ነገር ግልጽ አድርጎታል” በማለት ከዚህ በኋላ  እርዳታ አቁርጠው የነበሩ አባል አገሮች ለድርጅቱ የሚሰጡትን እርዳታ እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ሚስተር ቦርየል ገልጸዋል።

በራፍ የተከፈተው ጦርነት ሊያስከትል የሚችለው ሰብአዊ ቀውስ

ይሁን እንጂ እስራኤል ሀማስ ተቀብሎታል የተባለውን የተኩስ ማቆም ስምምነት ውድቅ ማድረጓ ብቻ ሳይሆን ከመላ የጋዛ ሰርጥ የተፈናቀሉ ካንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤሞች በተከማቹባት የራፋህ ከተማ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯ የሚያሳዝን መሆኑን ሚስተር ቦርየል በግልጽ ነው የተናገሩት።

የጋዛ ተፈናቃዮች በራፋ
እስራኤል የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማሳሰቢያ ችላ በማለት በራፋ የጀመረችው ዘመቻ እንዳሳሰባቸው ጆሴፕ ቦሬል ተናግረዋል። ምስል AFP

“የሚያሳዝነው ነገር የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ አልተደረሰም። ሃማስ የቀረበውን የተኩስ ማቆም ስምምነት ተቀብሏል፤ እስራኤል ግን ሀሳቡን ውድቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በራፋ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳትከፍት ከአሜሪካ፤ የአውሮፓ ህብረት እና ከአለማቀፉ ማህብረሰብ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ዘመቻ ከፍታለች” በማለት 600 ሺ ህጻናት በሚገኙባት ጋዛ ሌላ ሰብአዊ ትራጄዲ ሊከሰት እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዉሳኔ

ሚስተር ቦርየል አንዳንድ የህብረቱ አባል አገሮች በእስራኤል ላይ ባላቸው አቋም ግራ የተጋቡ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫቸው አንጸባርቀዋል። የዓለማቀፉ ፍርድቤት በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ ክስ ሲመስርት ደስተኛ የነበሩ አባል አገሮች፤ በእስራኤል እና መሪዎቿ ላይ ተመሳሳይ ርምጃ እንዳይታሰብ ማሳሰባቸው ግራ የሚያጋባ መሆኑን በግልጽ ተናገረዋል።

ትኩረት የሳበው የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ

“አለማቀፉ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ ላይ ክስ ሲመስረት እናደንቃለን። የየፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማንም ይሁን በማን መደገፍና ማክበር ነው የሚገባን፤ በተጻራሪው ግን በእስራኤል ላይ ሲሆን በፍርድ ቤቱ ዳኞች ላይ ጫና ማድረግ እና ማስፈራራት ተገቢ አይደለም” በማለት አባል አገሮች በአለማቀፍ ህግ እና ፍትህ ላይ ግልጽ እና ወጥ አቋም ሊያራምዱ ይገባል ሲሉ ሚስተር ቦርየል ወቀሳ ማሳሰቢያቸውን ጋዜጣዊ መገለጫ በሰጡበት ወቅት አስምተዋል።

ገብያው ንጉሤ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር